አዲሲቱ ጋዛ
ሄዷል፤ ጊዜው ሞቷል፤
በእናትህ ማሕፀን፤ መንጋለል ይበቃል።
አንተ ፅንሱ ልጄ፤ ገስግስ ድረስልኝ፤
ናፍቄህ አይደለም፤ እኔ እምልህ ናልኝ፤
ጦርነት ነው እልቂት፤ አንተን እሚያስጠራኝ።
ሳታያት እንዳትቀር፤ ፈራሁኝ አገርክን፤
እኔ እንዳለምኩልህ፤ እንዳልሆነች ሳትሆን።
…
ሃገርህ ደርሶ አፈር አይደለችም ባህር ብቻ፤
እጣችንን ተንብያ፤ ያየች የሞቷን መባቻ።
ሃገርህ ህዝብህ ናት፤
ቅረባት እወቃት፤
ፈንጂው ሳያፈርሳት።
ፍርስራሹን ሰውነት፤ ለመሰብሰብ ሳልሰቃይ
የጠፉትን ውብ ሰዎች፤ ንፁሃንን ላንተ ላሳይ፤
አንተን የመሰሉ፤ ህፃናት ያሏቸው
ከበረዶው የሬሳ ቤት፤ የሚያስመልጧቸው፤
እጓለ ሙውታን፤ በየውርጅብኙ ለጨዋታ ዘላይ
የሙጥኝ ያሉ ህይወትን፤ በቀጭኗ ገመድ ላይ።
…
ከረፈደ ከዘገየህ፤
ላታምነኝ ትችላለህ።
ትላለህ ሃገሬ መሬት ናት
ህዝብ የሌላት ያልነበራት።
እኛም እንመስልሃለን፤
እዚህ በወል ያልነበርን።
በድርብ ስደት ተሰቅይተን፤
በክፉ ዕጣችን አመፅን፤
በሰባ አምስት አመታት፤ በምሬቱ ተንገፈገፍን፤
ኑሯችን ጨርሶ ቢመክን፤
ተስፋችን ቢጠይምብን።
…
አውቃለሁ ሸክምህ ከመርግ ይገዝፋል፤
ልትቋቋመው ይከብዳል።
ይቅር በለኝ አባተትኩህ፤ አስቀጨነኩህ በፍርሃት፤
ምጤ ሆኖ እንደ እናት ሰስ፤ አውሬ እንዳስጨነቃት፤
ፈርቻለሁ ቢከቡኝ፤ ጅቦቹ ቢዞሩኝ፤
አድብተው ከጎሬ፤ ልጄን እንዳይነጥቁኝ።
እና ልጄ ክነፍ ብረር፤
ና ተወለድ ሩጥ ፍጠን፤
እንዳይበላኝ ፀፀት፤ እንዳይገለኝ ሰቀቀን።
…
ትላንትና ማታ፤ ተስፋ ማጣት አዛለኝ፤
ፀጥታ፤ ፀጥታ ይሁን አልኩኝ።
አሁን ይሄ ከሱ ጋራ፤ እንዴት ብሎ ይገናኛል?
የልጄ ስስ ትንፋሽ፤ ከገዘፈው ወጀብ በምን ይማሰላል?
ግና ዛሬ ዳግም ፊት እንዳይ ተፈረደብኝ፤
ፀጥታዬን ሰብሬ፤ መርዶ ነጋሪ ሆንኩኝ፡
አጋዩት፤ በፈንጂ አደባዩት፤
የጋዛን ባፕቲስት ሃኪም ቤት።
ከአምስት መቶ ሰለባዎች ከሞቱት ከቆሳሰሉት
አንድ ህፃን ልጅ ነበረ፤ ወንድሙን ፍለጋ እሚዋትት፤
ጭንቅላቱ ተገምሶ፣ የልጅ አናቱ ተበርቅሶ፤
አይኖቹን አፍጥጦ፣ እሚጣራ በደም ርሶ።
“ወንድምዬ! እታይሃለው?” እያለ በጣር ቢጣራም፤
ወንድሙን አያይም፤ እንደ አበደው ዓለም፤
ለሁለት ሰዓታት፤ አውግዞና ከሶ ከዚያ እንደሚተኛው፤
ኋላ እንደሚረሳው፤
ወንድሙን ይረሳል፤
እንዳያይ ይሆናል።
…
እኔ ምን አፍ አለኝ? አሁን ምን ልበለው?
እልቂትና ጥፋት እትማማች ናቸው።
ወዲህ አይጠረቁ፣ ወዲያም ብርቱ ሆነው፤
ይደቀድቁኛል እስኪንቀጠቀጡ ከናፍሬ ዝለው፤
እስኪንጠባጠቡ ተመሳሳይ ቃላት፤
ለአስክሬን ስያሜ ለሞተ ሰውነት።
በጦርነት ሰዓት፤ የቱንም ገጣሚ ፈፅሞ አትመኑት፤
ቀርፋፋ እንደ ኤሊ፤ ጉዞው ነው የዝግመት።
ከጥንቸልም የፈጠነን፤ የጭፍጨፋ እሳት ሰደድ፤
ላይሆንለት የሚከተል፤ ላይደርስበት የሚያሳድድ።
ኤሊው ሲሳብ ከጋት ስንዝር፤
ጥንቸል ሲዘል ከወንጀል ሰፈር፣ ወንጀል ሰፈር፤
ሲያዳርስ፤ አገሩን ሲያጥን፤
እስከ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን፤
እግዜር እያየ እስካጋዩት
መስጊዱም ትቢያ ሲሆን፤ አይቶ በመጣው አምላክ ፊት።
እሱን አምነው ተጠልለው፤ መድህን አገኘን ባሉበት።
የት ይሆን መድህኑ፤ አዳኙ የት አለ?
በሰማያት ያለው አባት፤ አውሮፕላኑ ከሆነ።
አምሳያ የሌለው፤ ተተካካይ ተወዳዳሪ፤
ከገዳያችን ከእሱ በቀር፤ ከአውሮፕላኑ አብራሪ።
ሆኖም ተፍፃሜቱ የጥቃቱ፤
የእኛ መውደቅ ነው ከፊቱ።
መስቀል ላይ ነህ አሁን ልጄ፤ አንተን ይስፋህ አልልህም፤
አግዳሚና ወራጁ፤ ለነቢያቱ አይጠብም።
አምላክ ሁሉን ያውቃል፤
አንተ እና መሳዮችህ፤ ንፁሃን ፅንሶች ግና፤
ልታውቁት ይሆናል ገና።
Amharic translation of Marwan Makhoul’s poem, New Gaza, by Surafel Wondimu Abebe.
Article by: